WORLD PARKINSON DAY IN ETHIOPIA
መድኃኒት በሌለው የፓርኪንሰን ህመም የሚሰቃዩ ኢትዮጵያውያን
(ይትባረክ ዋለልኝ)
#PPSO-E | የፓርኪንሰን ህመም በዓለም ደረጃ ለ26ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ11ኛ ጊዜ ዛሬ በሐገር ፍቅር ቲያትር ቤት በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶች ተከብሯል::
በዚህ ዝግጅት ላይ ገጣሚ ኤፍሬም ስዩምና ገጣሚና ተዋናይት ትዕግስት ዓለሙ ግጥምና መነባንቦችን ሲያቀርቡ በዚሁ በሽታ ዙሪያ የተዘጋጀ አጭር ድራማና ዶክመንተሪ ፊልም ቀርቧል::
በተጨማሪም ፓርኪንሰን ህመም ለሚሰቃዩ አረጋዊያንና ድጋፍና እገዛ ላደረጉ ቤተሰቦች እንዲሁም ለዚሁ ድርጅት ድጋፋቸውን ላደረጉ ድርጅቶች ከረ/ፕ ነብዩ ባዬ እጅ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል::
ላለፉት አመታት የዚሁ ድርጅት የክብር እምባሳደር ሆና ለህብረተስቡ ስለበሽታው የግንዛቤ ስራ ስትሰራ የነበረችው አርቲስት ሐረገወይን አሰፋ በቀጣይ ዓመታትም የክብር አምባሳደር ሆና በቀጣይነት ከድርጅቱ ጋር እንደምትሰራ ገልፃለች::
በዚህ ዝግጅት ላይ በበሽታው የተያዙ አረጋዊያን በርካታ እርቲስቶችና ጋዜጠኞች እንዲሁም የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል::
የፓርኪንሰን ህመም መንስዔው በውል የማይታወቅ የእንቅስቃሴን መገደብ ምልክቶችን ይዞ የሚመጣ በጣም ዘለግ ላለ ጊዜ ከታካሚው ጋር ሊሄድ የሚችል (Chronic illness) የነርቭ ህመም ነው::
መድሃኒት የሌለው ይህ በሽታ የሚያጠቃቸው እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑትን ነው:: በሐገራችንም በዚሁ በሽታ ተይዘው እቤት የዋሉ የአልጋ ቁራኛ የሆኑ በርካታ ናቸው::
ከዛሬ 12 ዓመት በፊት በዚሁ በሽታ ተጠቂ የሆኑት ወ/ሮ ክብራ ከበደ የፓርኪንሰን ፔሸንት ሳፓርት ኦርጋናይዜሽን መስርተው ብዙዎቹን በዚሁ በሽታ የተጎዱ ኢትዮጵያውያንን መደገፍና ህክምና ማድረግ ጀመሩ::
ዛሬ በርካታ በዚሁ ህመም የሚሰቃዩ አዛውንቶችን የፓርኪንሰን ፔሸንት ሳፓርት ኦርጋናይዜሽን ድጋፍና እገዛ እያደረገ ይገኛል::
የድርጅቱ መስራች የሆኑት ወ/ሮ ክብራ ከበደ የ2014 የበጎሰው ሽልማት ተሸላሚ ናቸው::